ከቍርስ በኋላ ቅዱስ ቦታ በሆነው በደብረ ጽዮን (2ሳሙ15፣30 ማር 11፣1 ሐዋ 1፣12) ጕብኝታችንን እንጀምራለን። በመቀጠል ጌታ የደቀ መዛሙርቱን እግር ወዳጠበበትና ከነርሱም ጋር የመጨረሻዋን የፋሲካን ራት ወደበሉበት ደርብ/ቤት እናቀናለን(ዮሐ13፡4)፤ ከዚያም ወደ ንጉሥ ዳዊት የመቃብር ሥፍራና ቅድስት ድንግል ማርያም ወዳረፈችበት ወደ ዶርሚሽን ቤተክርስቲያን እንቀጥላለን። በጽዮን በር በኩል ወደ ጥንታዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ እንገባና የአይሁድ ብቸኛ ቅዱስ ቦታ፣ ለሙስሊሞች ደግሞ ሦስተኛው ቅዱስ ቦታ የሆነውን ምዕራባዊውን የቤተ መቅደስ ክፍል እንጎበኛለን፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ የጸሎተ ሐሙስ ሥርዐትን ለመካፈል ወደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን። ራትና አዳራችን በኢየሩሳሌም ይሆናል።